
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን መንግሥታቸው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንደሚያደርግ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ቅዳሜ ጥር 28/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ መካሄድ በጀመረው በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ነው።
በንግግራቸው ያለፈው አንድ ዓመት ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ ችግር በባህሪው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ውስጣዊ ጉዳይ ነበር” በማለት “የውጭ ኃይሎች በነበራቸው ሚና” ምክንያት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገውታል ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በተመለከተ በንግግራቸው እንዳመለከቱት ምንም እንኳን ከተቃራኒው ወገን ግትርነት ቢኖርም፣ መንግሥታቸው የሚደርስን የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።
ከግጭቱ አካባቢ በተናጠል ሠራዊታቸውን ማስወጣታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መልካም ፈቃደኝነትን ለማሳየትና ለሰላም አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ዋነኛ ተጠርጣሪዎችን መንግሥት ከእስር እንደለቀቀ በመግለጽ “በአገራችን ሰላም ለማስፈን የማንፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ካለው ጽኑ አቋም አኳያ ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ የሚያስችል መድረክ በማቋቋም ሕጋዊ መሠረት ያለው ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሁልጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አገራቸው በገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ ወቅት የአፍሪካ አገራት ላሳዩት ድጋፍ፣ አጋርነት አና መረዳት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ የሆነውን በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ የአፍሪካ ሕብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካዩ አድርጎ በመሰየም የማሸማገል ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መሪዎች መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር አየተካሄደ መሆኑ የተነገረ ሲሆን አስካሁን ግን ምንም በይፋ የተነገረ ውጤት የለም።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በተገቢው መልኩ እየተወከለች እንዳልሆነ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ቅዳሜ ጥር 28/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ መካሄድ በጀመረው በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ነው።
የአፍሪካ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በትክክል ሊደመጥ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሰራር እንዲሻሻልና አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ለማድረግ የሚሰራበት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በአካል ሳይሰበሰብ የቆየው የሕብረቱ ጉባ ኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው።