
አሸባሪው ሸኔ በጊዳሚ ወረዳ 168 ንጹሐንን መግደሉን በኦሮሚያ ክልል የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ። መንግሥት በወሰደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ወረዳው ሙሉ በሙሉ ከአሸባሪው ሸኔ ነጻ መውጣቱ ተገልጿል።
የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳደር ተወካይና የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብሣ በሻ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በጊዳሚ ወረዳ አሸባሪው ሸኔ ዘግናኝ ግድያዎችንና የንብረት ውድመት ፈጽሟል።
በወረዳው በተለያዩ ቦታዎች 81 ሰዎችን እንዲሁም በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ 87 ሰዎችን በድምሩ168 ንጹሐን መገደላቸውን ገልጸዋል። አሸባሪው ሸኔ በወረዳው በቆየበት ጊዜ 30 የመንግሥት ተቋማትን ንብረቶችን ማውደሙንና ዝርፊያ መፈጸሙን አስታውቀዋል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎች ፣ኮምፒውተሮችና ሰነዶች ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል። የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ ከተማ ማዘጋጃ ቤትና ፖሊስ ጣቢያንም ማቃጠሉን ገልጸዋል። የሽብር ቡድኑ በትምህርት ዘርፉና በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በወረዳው የሚገኙ 45 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በስድስት ጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችም በአሸባሪው ሸኔ እንዲቋረጡ ተደርጓል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በአካባቢው በፈጸመው ጥቃት 20 ሺ 54 ሠራተኞች ከሥራ ገበታ ውጪ ሲሆኑ፤ በወረዳው የሚኖሩ ሰዎችም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሆነዋል ብለዋል። አሸባሪው በቁጥጥር ሥር ያሚያውሏቸውን ሰዎች ከአምስት ሺ እስከ ስምንት ሺ ብር በመጠየቅ ኅብረተሰቡን ሲያሰቃይ መቆየቱንም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኢብሣ ገለጻ፤ የዞኑ ምክር ቤት ከጸጥታ አካላት፣ ሚሊሻ፣ ልዩ ኃይልና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት በተደረገው ኦፕሬሽን ጊዳሚ ወረዳን ከአሸባሪው ሸኔ ሙሉ በሙሉ ነጻ ማውጣት ተችሏል። ኦፕሬሽኑን ተከትሎ መንግሥት የሕዝቡን ስነልቦና የወደሙትን ንብረቶች ወደነበረበት ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነውም ብለዋል።
በዞኑ አቅም እስከ አሁን በተደረገው ጥረት ተቋርጦ የነበረው አገር አቀፍ ፈተና አንድ ሺ 553 ተማሪዎች ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል። በሶስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁለት ጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል። ለኅብረተሰቡ ፈጣንና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የአደጋውን ጥልቀትና ክብደት ለመለየት የሚያስችሉ መረጃዎችን ለማጠናከር ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሮችን የመለየት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም አንስተዋል።
ዞኑ በ30 ሴክተሮች የወደሙበት ንብረቶችን አሟልቶ ወደ መደበኛ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት እንዲመለሱ ለማድረግ 15 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ሙሉ በሙሉ ለማሟላት አቅም እንደሚያጥረው ገልጸዋል። በጊዳሚ ወረዳ የተመዘገበው ድል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዞኑ ሕዝብ፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ተቀናጅቶ አንድነቱን አጠናክሮ አሸባሪውን ሸኔ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።