
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በኢትዮ-ጀቡቲ አዉራ መንገድ ላይ ወደምትገኘዉ ሰርዶ የፍተሻ ኬላ መቃረቡን የአፋር ክልል መስተዳድር አስታወቀ።ሰርዶ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር በሚያገናኘዉ አዉራ መንገድ ላይ የምትገኝ የፍተሻ ኬላ ናት።
ሮይተር ዜና አገልግሎት የአፋር ክልል መስተዳድር መግለጫን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ሕወሓት በአፋር ክልል አዲስ በከፈተዉ ጥቃት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር 3 መቶ ሺሕ ደርሷል።መግለጫዉ እንደሚለዉ የሕወሓት ታጣቂዎች በሚያወነጭፉት ከባድ መሳሪያ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ የተለያዩ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል።
ታጣቂዎቹ በየደረሱበት አካባቢ የሚገኙ ሐብትና ንብረቶችን መዝረፋቸዉንም መግለጫዉ አትቷል።አፋር ክልል ዉስጥ የሚደረገዉ ጦርነት ወደ ትግራይ የተላከ የዕርዳታ ዕሕል ለክልሉ ሕዝብ እንዳይደርስ ማደናቀፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል።
የአፋር ክልላዊ መንግስት መግለጫ እንደሚለዉ አሁንም በአምስት ወረዳዎችና አብላ ከተማ ዉስጥ ዉጊያ እንደቀቀጠለ ነዉ። ከቀናት በፊት ህወሓት አዲስ ጦርነት በከፈተባቸው መጋሌ እና ኮነባ በተባሉ ሁለት የአፋር ክልል አካባቢዎች በከባድ መሣርያ በፈፀመው ጥቃት ከሦስት መቶ ሺህ የሚበልጡ ዜጎች መፈናቀላቸው ተገለጸ። አካባቢዎቹም በህወሃት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአፋር ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአፋር ክልል ዳግም ያገረሸውን ጦርነት አስመልክቶ ከፌደራል መንግሥት መረጃ ለማድረግ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ የድሬደዋው ዘጋቢያችን መሳይ ተክሉ አመልክቷል። መንግሥት በሽብርኝነት የፈረጀው ህወሓት በአፋር የጀመረውን ጦርነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እየተገለፀ ባለበት በዚህ ጊዜ አዲስ ጥቃት የተከፈተባቸው ሁለት አካባቢዎች በህወሃት ታጣቂዎች መያዛቸው ተመልክቷል።