
የአማሮ ልዩ ወረዳ የሰላምና ፀጥታ ጽ/ ቤት ለዶቼ ቨለ ሬድዮ በሰጠው ቃል ፥ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት በጫኑት ሸቀጥ ላይ ሰዎችን አሳፍረው ከዲላ ከተማ ወደ አማሮ ኬሌ ሲጓዙ በነበሩ ኤፍ- ኤስ- አር የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ነው።
ጥቃቱን ትናንት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ የደረሰ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ውስጥ በተለምዶ የመከራ ዳገት በተባለ አካባቢ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ መቶ አለቃ ስላሴ ሽሎ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሶስት ሰዎች የአንደኛው ተሽከርካሪ ሾፌር ፤ ረዳቱና አንድ መንገደኛ ሲሆኑ በሌላኛው ተሽከርካሪ ላይ የነበሩ አራት ሰዎች ደግሞ በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን ገልፀዋል።
3ቱም ተሽከርካሪዎች ከዲላ በተነሱበት ወቅት በያዙት ጭነት ላይ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን ጭነው እንደነበረ የጠቀሱት ሃላፊው ታጣቂዎቹ መተኮስ እንደጀመሩ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከተሽከርካሪዎቹ ላይ በመዝለል ወደ ጫካ መሸሻቸውንና አስከአሁንም ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ አስረድተዋል።
ጥቃት ፈፃሚዎች ታጣቂዎቹ በመንገደኞቹ ላይ ካደረሱት ግድያ በተጨማሪ ንብረትነቻው የግለሰብ ነጋዴዎች የሆኑና በተሽከርካሪዎቹ ተጭነው የነበሩ ልዩ ልዩ ሸቀጣሸቀጦችንም ሙሉ በሙሉ መዘረፉቸውንም ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት የ3ቱን ሰዎች አስክሬን ወደ አማሮ ኬሌ ከተማ በማምጣት ዛሬ ቀትር የቀብር ሥነስረዓታቸው መከናወኑን የገለፁት የመቶ አለቃ ስላሴ የቆሰሉ ሰዎች ደግሞ በህክምና ተቋም ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል ሲሉ ለሬድዮ ጣቢያው ተናግረዋል።