
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ጥቅምት ትናንት ባደረገው የአስፈጻሚ አካላት ሹመት ድልድል ከተቀዋሚው የቤንሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ የሾማቸውን ሁለት አባላት እንዳነሳ ከክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ ፌስቡክ ገጽ ተመልክተናል።
ከሃላፊነት የተነሱት ባለፈው ጥቅምት የክልሉ ገጠር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው የተሾሙት የንቅናቄው ሊቀመንበር አብዱልሰላም ሸንገል እና ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊነት የተሾሙት የንቅናቄው ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ መሐመድ እስማዔልን ናቸው።
ሁለቱ የንቅናቄው አመራሮች ከሥልጣን የተነሱት፣ ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው እንደሆነ የክልሉ ምንጮች ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። ንቅናቄው በበኩሉ የፖለቲካ ሹመቱን ከጅምሩም እንዳልተቀበለው ገልጧል።