
መስከረም 08/1976 ዓ.ም የተወለደችው ሰብለ፣ በቀድሞው የደቡብ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ እና የሁለተኛ ዲግሪዋን ከዩኒቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተመርቃ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ስትሰራ ቆይታለች። ሰብለ በሁለቱም የትምህርት ግዜ ቆይታዋ የከፍተኛ የማዕረግ ተመራቂ እንደነበረች እናም የትምህርት ሕይወቷ ስኬታማ እንደነበረ ንጉሴ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አማካሪ የሆነችው ትንሳኤ ታደለ ለቢቢሲ እንደገለፀችው የሰብለ ቤተሰቦች የአካሏ 40 በመቶ ስለመቃጠሉ አስረድተውናል ትላለች።
የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አማካሪዋ ትንሳኤ ጥቃቱን አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መያዙን ለቢቢሲ ገልጻለች። ሕይወቷ እስኪያልፍ ድረስም በሕብረት ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት የሰው ሀብት አስተዳደር ክፍል ውስጥ በኃላፊነት ስትሰራ እንደነበር ወንድሟ ይናገራል።
ሰብለ ንጉሤ፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ጥቃቱ እንደተፈፀመባት ወንድሟ ያዕቆብ ያስታውሳል። ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የጠባቸው መነሻ የነበረው አምሽቶ መጥቶ በር አልከፈትሽልኝም የሚል እንደነበር የሚገልፀው ያዕቆብ፣ በቅድሚያ ፊቷን በቁልፍ በመምታት፣ አስከትሎም በስለት በመውጋት በስተመጨረሻም ሳኒታይዘር ገላዋ ላይ አርከፍክፎ በእሳት እንዳቃጠላት ይናገራል።
ሰብለ ሆስፒታል በነበረችበት ወቅት ይህንን ቃሏን ለሦስት የቤተሰቧ አባላት እንዲሁም ፖሊስ መናገሯን ጨምሮ ገልጿል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አማካሪ የሆነችው ትንሳኤ ታደለ ለቢቢሲ እንደገለፀችው፣ ሰብለ ላይ የደረሰውን ጉዳት ከሆስፒታል ማስረጃ እና ከቤተሰቦቿ እንደተረዱት የሰውነቷ 40 በመቶ ያህል ተቃጥሏል።
ሰብለ ላይ በእሳት መቃጠል ብቻ ሳይሆን ድብደባ እና በስለት መወጋትም እንደደረሰባት ከቤተሰቦቿ መረዳታቸውን ጨምራ ገልፃለች። ሰብለ ሆስፒታል ከገባችበት ዕለት ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሦስት ቀናት ውስጥ ራሷን ታውቅ እንደነበር የሚናገረው ያዕቆብ በበኩሉ ከዚያ በኋላ ግን ሕመሟ በመበርታቱ መናገር አለመቻሏን አመልክቷል።
ሰብለ እና የወንድ ጓደኛዋ አሁን ወንጀል የተፈፀመበት ቤት ውስጥ የኖሩት ሁለት ወር ከአስራ አምስት ቀን ብቻ መሆኑን የሚያስታውሰው ያዕቆብ፣ ሰብለ ለቤተሰቧ ለብቻዋ ተከራይታ እንደምትኖር እንጂ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር እንደምትኖር ተናግራ እንደማታውቅ ይህም ነገሮች መስመር ከያዙ በኋላ የማሳወቅ ባህሪዋ ቀድሞም አብሯት የነበረ መሆኑን ይገልጻል።
ሰብለ እና ጓደኛዋ ለምን ያህል ጊዜ በጓደኝነት እንደቆዩ እንደማያውቅ የሚናገረው ያዕቆብ፣ ሕይወቷ ካለፈ ከአስር ቀን በኋላ አንድ ጓደኛዋ ከዚህ ቀደም ድብደባ እንደፈጸመባትና ይህንንም አጫውታት እንደነበር መናገሯን ይገልጻል።
ያዕቆብ ንጉሤ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እድሜ፣ ኢኮኖሚ፣ የትምህርት ደረጃ እንደማይወስነው እና ጥቃት በማንኛውም ሴት ላይ የሚደርስ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት በእህቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት በዋቢነት ይጠቅሳል።
ጥቃት ቀስ እያለ እንደሚያድግ እና በአንድ ጊዜ ወደ ግድያ ሊደርስ ይችላል ብሎ እንደማያምን የሚናገረው ያዕቆብ፣ ሌሎች ሴቶች ከአጋራቸው በኩል የሚሰነዘርን የመጀመሪያውን ጥቃት በአስተዋሉ ጊዜ ለሚመለከታቸው አካላት፣ ቤተሰብን ጨምሮ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው ይላል።
ሰብለ እናት እና አባቷን የምትጦር፣ ለታናናሾቿ አርዓያ የነበረች ሴት ነበረች የሚለው ያዕቆብ፤ ለቤተሰቧ የስኬት ተምሳሌት እንደሆነች ይጠቅሳል። የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አማካሪዋ ትንሳኤ ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መያዙን ለቢቢሲ ገልጻለች።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ማክሰኞ ጥር 24/2014 ዓ.ም በተፈጸመባት አሰቃቂ ጥቃት በእሳት ተቃጥላ ሕይወቷ ያለፈውን ሰብለ ንጉሤን የሚዘክር ሥነ ሥርዓት አዘጋጅተው ነበር። በዚህ የሻማ ማብራት ዝግጅት ላይ ቤተሰቦቿ፣ የሥራ ባልደረቦቿና የሲቪክ ማኅበራት አመራሮች እና ኃላፊዎች መገኘታቸውን ትንሳኤ ትገልጻለች።
የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓቱን ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት ስታስረዳም አንድም ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ፣ ሰዎች ስለፍትህ መጮህ ካለባቸው እንደ እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ እና ቤተሰቦቿን ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳየት ነው ብላለች።
ከዚህ በፊት ሰብለ የደረሰባት ጥቃት እንጂ ማን ናት በሚል በአግባቡ አለመነገሩን አስታውሳ እርሷን ለመዘከርም ያለመ እንደሆነ ገልጻለች። በሴቶች ላይ የተለያዩ አይነት ጥቃቶች ሲደርሱ በመገናኛ ብዙኃን እንደሚሰማ እንዲሁም ወደ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እንደሚመጡ አስታውሳ፣ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ቢሮ ከፍተው እንደሚንቀሳቀሱ ታስታውሳለች።
ነጻ የሕግ ድጋፍ በሚሰጡባቸው ቢሮዎች በአጠቃላይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ በርካታ ጥቃቶች እንደሚመጡ አስታውሳ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶባቸው የሚመጡ ሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ መሆኑን አመልክታለች።
ይህ የቤት ውስጥ ጥቃት አካላዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን በርካታ መልክ እንዳለው የምታስረዳው ትንሳኤ፣ ጥቃቶች በቅርብ ሰዎች የሚደርሱ እንደሆኑና ጥቃቶች እንዲቀንስ፣ በተለይ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ ለማድረግ አጥቂዎችን ማሰብ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።
ለዚህም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት እና ለመለወጥ በማኅበራቸው በኩል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ማኅበራትም ሊሳተፉበት እንደሚገባ ገልጻለች። ማኅበረሰቡም ቢሆን ልጆቹን የሚያሳድግበት ሥነልቦና፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት እና የሕግ አካላት በየፊናቸው መስራት የሚኖርባች ሥራዎች መኖራቸውን ታስታውሳለች።
ጥቃት ፈጻሚዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላም አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲሰጥ ማድረግ ሌላው ሊተኮርበት የሚገባ ነገር መሆኑን የምትገለጸው ትንሳኤ፤ የሴቶች ጥቃት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከመሆኑ አኳያ ለመብቶች መከበር፣ በሴቶች ላይ የሚሰሩ ማኅበራት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ገልጻለች። ቢቢሲ