
ዛሬ ፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ-ሽብር እና የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረቡት የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ጨምሮ 17 ተከሳሾች ተቃውሞ አሰምተዋል።
እነ አቶ አብዲ ኢሌ ከኛ ጋር ታስረው የነበሩት እስረኞች ተፈተው እኛ የምንታሰርበት ምክንያት የለም ሲሉ ነው ተቃውሞ ያሰሙት። አቶ አብዲ መሀመድ እጃቸውን በማንሳት ይህን ተናግረዋል ” ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት አንቀርብም እኛ ከስር ከተፈቱ ግለሰቦች የተለየ ምንም ወንጀል አልፈጸምንም። ስለዚህ ሌሎች ዕስረኞች ተፈተው እኛ ታስረን ፍርድ ቤት የምንቀርብበት ምክንያት የለም።
ከአማራ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ከትግራይ እና ከሌሎችም ከተፈጸመው ወንጀል የኛ በምን ይለያል ? ግድያ በተፈጸመበት ሁኔታ ሌሎች ሳይጠየቁ እኛ ብቻ የምንታሰርበት ጉዳይ የለም። ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ እኛ ፍርድ ቤት አንቀርብም። ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ ይስጥበት ”
ከሳሽ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ይስጥበት እና ክርክሩ ይቀጥል ሲል ችሎቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ከእስር የተፈቱ እስረኞችን ክስ ያቋረጠው ፍትህ ሚኒስቴር መሆኑን ገልጿል።
አስተያየታቸዎውን ለፍትህ ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚችሉ የገለጸው ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ መርምሮ ተገቢውን ትዛዝ ለመስጠት ለፊታችን ሀሙስ የካቲት 3ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል። (የመረጃ ባለቤት ፦ ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ)