
ባለፉት ሦስት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ ማለትም በአራቱ የወለጋ ዞኖች ግድያዎች፣ የንብረት ውድመት እና ማፈናቀሎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ሆነው ከርመዋል።ይህ ግድያ፣ ንብረት ማውደም እና ማፈናቀል በአሁኑ ጊዜ ከወለጋ ወደ መካከለኛው የአገሪቱ ክፍል፤ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሸጋግሯል።ይህም መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመውና ‘ሸኔ’ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን የእንቅስቃሴ አቅጣጫ ጋር የተያያዘ ነው።
በምዕራብ ኦሮሚያ በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞን በስፋት እንደሚንቀሳቀስ ይነገር የነበረው ይህ ታጣቂ ቡድን በአሁኑ ጊዜ በበርካታ የምዕራብ ሾዋ ዞን አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ባለፉት ጥቂት ወራትም አምቦ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳዎች ንጹሃን የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች በግፍ ተገድለዋል፤ ቤታቸው ተቃጥሎ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የሁለቱ ብሔር ተወላጆች፣ የዓይን ምስክሮች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ በዞኑ ባለፉት ጥቂት ወራት መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ቡድን የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰንዝሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአማራ ብሔር ተወላጆችን ተገድለዋል። ይህን ተከትሎ የአማራ ተወላጆች በወሰዱት “የበቀል እርምጃ” በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች መገደላቸው ይነገራል።
ጫንዶ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ውስጥ የምትገኝ ቀበሌ ናት። ጫንዶ የተዘራባትን የምታበቅል በለምነት የታደለች ስፍራ ናት። በዚህም ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከወሎ አካባቢ ከ80 ያላነሱ አባ ወራዎች በአካባቢው እንዲሰፍር መደረጉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአካባቢው ቀድመው የነበሩ ነዋሪዎችና ኋላ ላይ ወደ አካባቢው የመጡት ሰዎች ለረጅም ዘመናት ያለ ችግር በሰላም የኖሩባት ጫንዶ፤ ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም. ላይ ግን አሰቃቂ ሁኔታን አስተናግዳለች።
በዕለተ ዓርብ የአንድ ዓመት ተኩል ታዳጊን ጨምሮ ከ20 ያላነሱ የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን ሦስት በጥቃቱ የቅርብ የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አበባው መኮንን የጫንዶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን በዚያን ዕለቱ ጥቃት 15 የቅርብ ዘመዶቹን አጥቷል። “ባለቤቴ ከእነ ልጆቻችን፣ ወንድሜ ከነ ልጆቹ፣ እህቴ ከነልጆቿ ተገድለዋል። ጎረቤቶቼም ተገድለዋል። ከእነርሱ ጋር በአጠቃላይ 25 ሰዎች ናቸው የተገደሉት” በማለት ከታኅሣሥ 22ቱ ግድያ በኋላ፤ “ብቻዬን ቀርቻለሁ” ሲሉ የገጠማቸውን መከራ ይናገራሉ።
የአካባቢው ሚሊሻ ታጣቂ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አበባው ወደ ቀበሌያቸው ከመጣው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ቡድኑ በጫንዶ ቀበሌ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት፤ “በቀበሌዋ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ሰፍረው በነበሩ የኦሮሚያ ሚሊሻ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ ነበር” ይላሉ አቶ አበባው። “ለ30 ደቂቃ ያህል ተታኩሰው እነሱን ጨርሰው ከመጡ በኋላ የአማራ ቤቶችን እየለዩ መግደል ጀምሩ” በማለት አበባው የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት እንደቻለው ታጣቂ ቡድኑ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ሰፍሮ አካባቢውን ሲጠብቅ በነበረው የክልሉ የሚሊሻ አባላት ላይ በተከፈተ ጥቃት ቢያንስ አምስቱ በዕለቱ ተገድለዋል። አበባውም ከትኩስ ልውውጡ በኋላ ከአካባቢው ሸሽቶ ሄዶ ሲመለስ፤ በቀበሌዋ ተወልደው ያደጉት ልጆቹ እና ባለቤቱን በሕይወት አላገኛቸውም። በታኅሣሥ 22ቱ ግድያ ወላጅ አባቱን እንዳጣ የሚናገረው ደግሞ ጀማል ሙሳ ነው።
“ከአማራነታችን በተጨማሪ እኛን ዒላማ ያደረጉበት ምክንያት ወንድሜ ሚሊሻ ነው። 15 ሰው የተገደለበት ቤተሰብ ውስጥም ሚሊሻ አለ” በማለት እንዴት በታጣቂ ቡድኑ ዓይን ውስጥ እንደገቡ ይናገራል። በተመሳሳይ ዑመር አበባው የተባለው ግለሰብ በጥቃቱ ወንድም እና እህቱን ጨምሮ ልጆቻቸው ያሉበት አምስት የቅርብ ቤተሰቦቹን አጥቷል።
ዑመር በጥቃቱ የተገደሉትን ሰዎች ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከለተ መልኩ መቅበር እንዳልቻሉ እና “በስንት ችግር በአንድ ጉድጓድ እስከ 6 ሰው ለመቅበር ተገደናል” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል። ይህ ጥቃት ከተፈጸመ ሳምንታት ቢያልፉም ጥቃቱን ተከትሎ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀበሌዋ እንዳልተመለሱ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በተለያዩ ስፍራዎች ተበታትነው የሚገኙ ሰዎችም ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ወገን ምንም አይነት የእርዳታ ድጋፍ ሳያገኙ በችግር ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ። “ከአሁን በኋላ ምን ተስፋ አለን? ቢወራ ቢወራ ምንም ለውጥ የለም። የወለጋው ወሬ ሆኖ ቀርቶ የለ? ከወሬ ያለፈ ነገር የለም። የእኛም መጨረሻ ይሄው ነው” በማለት ብሶቱን ገልጿል። ቢቢሲ