
በኤርትራ መንግስት በቁም እስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንዮስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው ተገለፀ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም (ተሚማ/አዲስ አበባ)
በኤርትራ መንግስት በቁም እስር ላይ የቆዩት የቀድሞው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው ተገለፀ።
በፈረንጆቹ 2004 ላይ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ በመሆን የተሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንዮስ መንበሩን ከያዙ ከሁለት ዓመታት በኋላ የኤርትራ መንግሥት ቄሶች ማሠሩን በመቃወማቸው ለቁም እሥር እንደበቁ ይነገራል።
ከዚህ ቀደም የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በስድስት ወንጀሎች እንደከሰሳቸው የተናገሩት አቡነ እንጦንዮስ ፤ ”ሕግ በመጣስ እኔን ሳያናግሩ ራሳቸው ከሳሽና ፈራጅ በመሆን ከፓትርያርክነት አውርደው ተራ መነኩሴ እንድሆን አደረጉኝ” ሲሉ ከፓትርያርክነት የተነሱበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
ቅዱስ ፓትርያርኩ ለበርካታ አመታት በቁም እስር ላይ ቆይተው ሐምሌ 2017 ላይ በከፍተኛ የፀጥታ ኃይል ታጅበው አስመራ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ንግግር እንዲያሰሙ ግን አልተፈቀደላቸውም።
እስከ አሁን ቅዱስ ፓትርያርኩ ያሉበት አድራሻ በውል የማይታወቅ ሲሆን መንግሥት ሕክምና የማግኘት መብታቸውን ገፏል እየተባለ ሲታማ የቆየ ቢሆንም በዛሬው ዕለት በውጭ ሀገር የሚገኙ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ገፆች የቅዱስ ፓትርያርኩን ከዚህ ዓለም ድካም ማረፍ አስታውቀዋል።
ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንዮስ ከሥልጣነ ፕትርክና መውረድ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ በመሆን የተሾሙ ቢሆንም አቡነ ዲዮስቆሮስ ዐረፍተ ዘመን የገታቸው መሆኑን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት በሥልጣነ ፕትርክናው ላይ ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ሢመተ ፕትርክናቸው ተፈፅሟል።ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል