
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው እንደፈለገው የተነገረው መምሕር ምሕረተአብ፣ ከቀናት በፊት ወደ ኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ባቀናበት ወቅት የጸጥታ አካላት ቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት በመሄድ ሊይዙት ሲሞክሩ በሌላ በር በማምለጥ ወደ ጋምቤላ ክልል ካቀና በኃላ ወደ አዲስ አበባ በመሳፈር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ እንግሊዝ ሀገር ማቅናቱን አምባ ዲጂታል ከምንጮቹ ሰምቷል።
ፖሊስ መምሕር ምሕረተአብ አሰፋን በቁጥጥር ስር ሊያውለው የነበረው ግጭት በመቀስቀስ ጠርጥሮት መሆኑ ታውቋል።የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአሁኑ ጊዜ መምሕር ምሕረተአብ አሰፋና አባሪዎቹ ያላቸውን 5 ግለሰቦች የባንክ ሒሳቦች ለመመርመር እንዲያስችለው ፍርድ ቤት ለባንኮቹ ትእዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል። ፖሊስ በተጨማሪም የግለሰቦቹ የባንክ ሒሳቦች እንዲታገዱለት ጠይቋል። ባለፉት ዓመታት ‘የማንቂያ ደወል’ በሚል ሃይማኖታዊ መርሐ ግብር የሚዘጋጀው መምሕሩ፣ በመሰናዶዎቹ በሃይማኖቶች መካከል ጥላቻን ይነዛል በሚል ክሶች ይቀርብበታል።